ESSS NEWS

ከአምሳ ሺህ ዓመታት ቆይታ በኋላ የተመለሰችው ኮሜት

በቅርቡ መነጋገሪያ ሆና የቆየችው C/2022 E3 ZTF የተሰኘችው ጅራታም ኮከብ (ኮሜት) ፣ ታኅሣሥ 29 ቀን 2020 በፓሎማር ኦብዘርቫቶሪ(Palomar Observatory) ውስጥ በZwicky Transient Facility ( C/2022 E3 ZTF) የተገኘች የረዥም ጊዜ (long-period) ጅራታም ኮከብ ናት ። C/2022 E3 ZTF ልዩ ጅራታም ኮከብ የሚያረጋት ባለፉት አስርት ዓመታት ከታዩት ደማቅ ጅራታም ኮከቦች መካከል አንዷ በመሆኗና የምርምር ጣቢያው ያገኘው የመጀመሪያው የረጅም ጊዜ(long-period) ጅራታም ኮከብ በመሆኗ ነው።

Long-period (የረጅም ጊዜ) ጅራታም ኮከቦች በምህዋራቸው ለመዞር እና ወደምድር ደግመው ለመመለስ ከ 200 እስከ 1 ሚልየን አመታት የሚፈጅባቸው ሲሆን፣ ይችህም C/2022 E3 ZTF የተሰኘች ጅራታም ኮከብ ለመጨረሻ ጊዜ ምድርን የጎበኘችው ከአምሳ ሺ አመታት በፊት የሰው ልጅ የበረዶውን ዘመን(Ice age) በሚጋፈጥበት ጊዜ ነበር፣ አፉን ያልፈታው የሰው ልጅ አንዲት አረንጓዴ የብርሃን ጮራን በሰማይ ላይ ይመለከታል። እኛም አምሳ ሺ ዓመታት በኋል የምርምራችን ልቀት አይሎ ምንነቷን ሳይሆን ለኛ የምትከፍተውን የምርምር በር በማሰብ አይኖቻችንን ወደ ሰማይ እንሰቅላለን፣ በጉጉትም እንመራመራለን።

የዚች ጅራታም ኮከቧ ምህዋር ወደ ፀሃይ ጠለል ያዘነበለ ሲሆን ከኔፕቱን ምህዋር እጅግ የራቀ ነው ። ይህም የሳይንስ ሊቃውንት ስለ መጀመሪያዎቹ ሥርዓተ ፀሐይ እንዲሁም ስለ ኩይፐር ቀበቶ (Kuiper Belt) አካላት ይበልጥ እንዲያጠኑና እንዲማሩ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል ። C/2022 E3 ZTF በምሽት ከምድር ገጽ ሊታዩ ከሚችሉ ጥቂት ጅራታም ኮከቦች አንዷ በመሆኗ ጠቀሜታዋ የጎላ ነው ። የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች በጥር 22 እና 25፣ 2015 ዓ.ም (Feb 1 and 2 ,2023) ላይ በሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ ውስጥ እንደምትታይ የተነበዩ ሲሆን ይችው አረንጓዴ ጅራታም ኮከብ በዛሬና በቀጣይ ቀናት ምሽቶች ለምድር ቀርባና ደምቃ የምትታይ ይሆናል። ኮሜቷን ለማየትም ፖላሪየስ(ሰሜናዊው ኮከብ) በሚታይበት የሰማይ ክፍል አከባቢ በአይን ፈልጎ ማግኘት ይቻላል።

በመጨረሻም C/2022 E3 ZTFን ጨምሮ ጅራታም ኮከቦች በሥርዓተ ፀሐይ ዝግመተ ለውጥ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ አስደናቂ ሰማያዊ አካላት ናቸው ። ጅራታም ኮከቦች ላይ የሚካሄዱት ጥናቶች ስለ አጽናፈ ዓለም አፈጣጠርና ዝግመተ ለውጥ ጠቃሚ የሆነ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ከመሆናቸውም በላይ ስለ እነዚህ ድንቅና የተፍጥሮ እንቁዎች ይበልጥ ለማወቅ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ይከፍታሉ።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ
ኢትዮጵያ ሳይንሳዊ ማህበረሰብ ትሆናለች!