ኢትዮጵያ እንድትሰይም እድሉ የተሰጣት የህዋ አካል

05/23/2019

በዘርፉ ኢትዮጵያ እያደረገች ላለችው ጥረትና ተሳትፎ እውቅና በመስጠት የህዋው የአለምአቀፉ ህብረት /International Astronomical Union/ በኛው ጋላክሲ ውስጥ የሚገኙትን በሳይንሳዊ መለያ HD16175  ተብሎ የሚታወቅ ኮኮብና በመለያ ቁጥር HD16175b ተብላ የምትታወቀዋ ፕላኔት ስርአት ኢትዮጵያ እንድትሰይም እድል በመሰጠቱ መላውን የኢትዮጵያ ህዝቦች እንኳን ደስ ያለን እንላለን፡፡  ይህንንም አስመልክቶ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ እና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዛሬ በሸራተን ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

 ይህ ኢትዮጵያ እንድትሰይም የተሰጠው ስርአት ውስጥ ያለው ኮኮብ 195.6 የብርሃን ዓመት ከእኛ ብትርቅም ከፀሐይ 1.34 ጊዜ የምትገዝፍ፣ ስፋቷ ደግሞ ከጸሃይ 1.66 ጊዜ ያህል የምትበልጥ እና ከሶስት እጥፍ በላይ ከጸሃይ የበለጠ የምታበራ መሆኗ ታውቋል። ይህችን ኮኮብ የምትዞራት ፕላኔት ደግሞ በተመሳሳይ ርቀት ስትገኝ በግዙፍነት ደግሞ ጁፒተር ከሚባለው ፕላኔት ከ 4.8 ግዜ በላይ ትበልጣለች። 

ለዚህ የህዋ አካውል የምንሰጠው ስያሜ ዝንተ ዓለም መጠሪያቸው ሆኖ ኢትዮጵያ የምትታወስበት በመሆኑ ታላቅ ክብር እና ኩራት እየተሰማን መሆኑን እየገጵን አለም አቀፉ የህዋው ማህበር   /IAU/ የስም አወጣጡን በተመለከተ የምንከተላቸውን ሂደቶች እና ስያሜውን ማሳወቅ ያለብንን ቀን ቆርጦ በማስቀመጡ ይህ የስም አወጣጥና አካሄዶች በሚቀጥለው ሳምንታት ውስጥ በሶሳይቲያችን እና በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ይገለፃል። 

በዚህ መሰረት አሰያየሙ በተቻለ መጠን ሰፊና ህዝባዊ ተሳትፎ ማግኘት ስላለበት መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ዩኒቨርስቲዎችና ሌሎች ትምህርትቤቶች፣ እንዲሁም ምሁራን፣ ተቋማት፣ እድሮች፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ወጣቶች፣ የሙያ ማህበራት፣ የገጠርና የከተማ ነዋሪዎችን ጨምሮ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለያዩ መንገዶች እንድትሳተፉ ሀገራዊ ጥሪ ቀርባል። 

ስለዚህም የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ቤተሰቦች ስም ለማውጣት እንድትዘጋጁ እናሳስባለን። 

Copyright © 2020 Ethiopian Space Science Society. Designed by Techno Bros